
ንሥር ብሮድካስት
ጥር 1/2015
ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በራስ ሆቴል፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እንግዶች በተገኙበት የተካሄደው የትብብር ስምምነት ሦስቱ ፓርቲዎች የምርጫ ጉዳዮችን ጨምሮ በብሔራዊ መግባባት እና የሰላም ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡
ትብብሩን አስመልክቶ አጭር መልዕክት እንደሚእንደሚከተለው ተያይዟል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ታላቅና በሌሎች የምትፈራ ሀገር ነበረች፡፡ የሥልጣኔ ማማ ላይ ደርሰው ከነበሩ ጥቂት ሀገራትም አንዷ ነበረች፡፡ ካልደረሱባት የማትደርስ የሰው የማትሻ፣ የራሷንም የማታስደፍር፣ በቀና የቀረቧትን በፍቅር የምታስተናግድ፣ በክፋት ያይዋትን በክርኗ የምታደቅ ኃያል ሀገር ነበረች፣ ናትም፡፡ ለጭቁኖችና በቅኝ ገዢዎች ሥር ለሚማቅቁት ተስፋን የምታጭር የነጻነት ቀንዲል፣…፡፡ ይሄ ወርቃማ የታሪክ አሻራ ተረስቶ ዛሬ ዛሬ ተረት ተረት ሊመስል ሩብ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለራሷ ሰላም ያጣች፣ ዜጎቿ የጎሪጥ የሚተያዩባት፣ የኢፍትሓዊነት፣ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ቸነፈር፣ ጉስቁልና ስደትና እርዛት መገለጫ ምድር ሆናለች፡፡ ብዙ እያላት ምንም የሌላት እየሆነች ነው፡፡ የዚህ ኹሉ ምስቅልቅል መነሾው ብዙና ሥር ሰደድ ቢሆንም ዋናው ግን ኹነኛ አመራር እና አስቻይ ሥርዓት ያለመዘርጋት ለመሆኑ እማኝ አይሻም፡፡
ይህን መልካም አመራር እና ሥርዓት ሊያዋልዱ ተስፋ የሚጣልባቸው ፓርቲዎች ተበታትነው መገኘታቸው ደግሞ አቅም ያለውና ተስፋ የሚጣልበት አማራጭ እንዳይኖር ከባድ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ሰብሰብ ሲሉም የፖለቲካችን ሾተላይ ይበላቸውና ይባስ ብለው የሕዝቡን ተስፋ አትንነውበት እነርሱኑ ለማሸማገል ይቀመጣል፡፡ አኹን ላይ ፖለቲካችን በገዢው ፓርቲ ጥንካሬ ሳይሆን በተቃዋሚው መበታተን/መበጣጠስና ይሄው ችግር በፈጠረው አዙሪት ውስጥ እየዳከረ ይገኛል፡፡ ዛሬ በእናት ፓርቲ፣ በመኢአድ እና በኢሕአፓ የሚፈረመው የትብብር ስምምነት ይሄን አባዜ ለመሻገር ያለመ ነው፡፡ ያለፈውን አንድ ዓመት በጋራ ሠርተናል፤ በሀገራችን ኹለንተናዊና ነባራዊ ሀቆች ዙሪያ በሳል ትችቶችንና አማራጭ ሀሳቦችን አቅርበናል፡፡ ይሄ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን እርስ በእርስ አስተዋውቆናል፤ ለዚህ ፍሬም አብቅቶናል፡፡ በዑደት ተገናኝተናል፣ መክረናል፣ ዘክረናል፣ ብዙዎችን ወደስብስባችን ዐውድማ ጠርተናል፡፡ ለጊዜው ኹኔታው ስላልፈቀደላቸው “ግዴለም ለጊዜው እኛ እንቅደምና…” ብለን ወደፊት ለፊት ወጥተናል፡፡ ዛሬ በይፋ የምንፈራረመው ትብብር እንዲህ ሀገርና ሕዝብ ጭንቅ ላይ በወደቁበት፣ የሕዝባችን ሞት ለርዕስነት’ኳ እየበቃ ባልሆነበት ጊዜ ተስፋ ለመሆን፣ በትብብር ቆመናል አለንልህ ለማለት፣ ለቀሪውም አርዓያ ለመሆን ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም የዛሬው የትብብር ስምምነት ፓርቲዎቻችን በሚከተሉት አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራና በትብብር እንዲሠሩ ማዕቀፋዊና ሞራላዊ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ በሀገራዊ መግባባት፣ በምርጫ፣ በሰላም ማስፈን እና መሰል ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋሞችን በማራመድ በሰላማዊ መንገድ በትብብር እንታገላለን፡፡ በተለይ በየዕለቱ ለሚሞተው እና በድርሱልኝ ሲቃ ለሚቃትተው ወገናችን ድምጽ በመሆን ከገባበት ችግር እንዲላቀቅ መሥራት ከግንባር ቀደም ተግባሮቻችን ዋናው ነው፡፡
በመጨረሻም ምሁራን፣ የፖለቲካ ልኂቃን፣ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ሲቪክ ተቋማት፣ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ሚዲያው ከሁሉም በላይ የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብራችን ይበልጥ እንዲያብብና እንዲጎመራ ኹለንተናዊ ድጋፉን እንዲያሳይ አበክረን እንጠይቃለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የትብብር ዐውድማችን ለኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት መሆኑን፣ መጥታችሁ በጋራ ጠምደን ያማረ ምርት እንድንወቃ፣ ኅብረታችን በብዙ ዓይነት ፈትል እንድንገምደው፣ ተበታትነን ለየብቻ ከምንሞት ሰብሰብ ብለን እንድንድን ወንድማዊ ጥሪያችንን ልናስተላልፍ እንወዳለን፡፡
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
ከእናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ትብብር የተላለፈ መልክት
==========================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://bit.ly/3No0s7x
FaceBook:https://www.facebook.com/Nisirbroadcasting
Telegram:https://t.me/nisirbroadcasting Website: https://nisirbroadcasting.com
Twitter:https://twitter.com/NISIRInternati1
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
ንሥር ብሮድካስትን በወዳጅነት ይከታተሉን።

