
ንሥር ብሮድካስት/ታህሳስ 14/2015
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ያለውን በደል ሁከት ቀስቃሽ ድርጊት በሕግና በሥርዓት እልባት እንዲያገኝ ለሚመለከተው አካል አቤቱታ በደብዳቤ እንዳሳወቀች ተገልጿል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ በጻፈው ደብዳቤ አንዳንድ ቤተ እምነት አስተማሪዎች የቤተ ክርስቲያናችንን የዘመናት ውለታ ዘንግተው ያለ ስሟ ስም በመስጠት፣ በማብጠልጠል፣ ማንኳሰስ እና ማጠልሸት እንዲሁም ሁከት ቀስቃሽ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸምን ሥራዬ ብለው ማከናወን ከጀመሩ መቆየታቸውን በማንሳት ይህንንም ተግባር በዝምታ ማለፍ የማትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን ገልጿል፡፡ በዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የድርጊቱን የወንጀል ይዘት በአግባቡ በማጤንና በመመርመር የወንጀል ክስ በመመሥረት አስተማሪ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እና ውጤቱን እንዲያሳውቅ ቤተ ክርስቲያን ጠይቃለች፡፡
በተጨማሪም ለኢፌዴሪ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በተጻፈው ደብዳቤ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት ማንኛውም የሃይማኖት ተኮር ሚዲያ የሚያሠራጫቸው ፕሮግራሞች ለሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች ተገቢ ክብር እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ ያለበት እንዲሁም የሚተላለፉ ፕሮግራሞችም ቢሆኑ የሌሎችን ሃይማኖቶች ወይም እምነት የሚያናኳስስ አለመሆኑን እና በሃይማኖቶች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ እንደሌለበት የተደነገገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ፓስተር ዮናታን አክሊሉ በማርሲል ቲቪ እንዲሁም ነቢይ እዩ ጩፋ በክራይሰስት አርሜ ቲቪ ላይ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት፣ አምልኮ፣ ክብር እና መልካም ስም በማጉደፍ የሚዲያ ሕግ በመጣስ በቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላይ የማይተካ ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ ቤተ ክርስቲያኗ አሳስባለች፡፡ ችግሩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የጉዳዩ አሳሳቢነትን በማጤን አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥም በአፅንዖት ጠይቃለች፡፡
====================================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://bit.ly/3No0s7x
FaceBook:https://www.facebook.com/Nisirbroadcasting
Telegram:https://t.me/nisirbroadcasting Website: https://nisirbroadcasting.com
Twitter:https://twitter.com/NISIRInternati1
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
ንሥር ብሮድካስትን በወዳጅነት ይከታተሉን።






