
ለ፳፮ዓመታት ታላቁ የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን በአስተዳዳሪነት ያገለገሉት መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ማርያም በተወለዱ በ፹፮ ዓመታቸው ዛሬ ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ማርያም ከአባታቸው አቶ ወ/ማርያም ተ/ሚካኤል እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወ/ኪዳን ኪዳኑ መስከረም ፲፮ ቀን ፲፱ ፴፬ ዓ.ም በአድዋ አውራጃ እንዳ አቡነ ኢዮሲያስ ገዳም ተወለዱ።
ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስም በእንዳ አቡነ ኢዮሲያስ ገዳም፣ በመካነ ሕይወት ጭህ ሥላሴ ገዳም (ተንቤን) ፣በመደራ አቡነ ገሪማ ገዳም ቅዳሴ፣ቅኔ፣ጸዋትወዜማ ተምረዋል።
በ፲፱፶፩ዓ.ም የመንኮሱት መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ማርያም በተለያዩ አህጉረ ስብከት በልዩልዩ የሥራ ዘርፎች ቅድስት ቤተክርስቲያናቸውን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ፲፱ ፹፮ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ የታላቁ ቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ በመሆን ተሹመው ገዳሙን ለ፳፮ዓመታት በታላቅ ትጋትና በፍጹም ብቃት በቅንነት፣በታማኝነትና በጽናት አገልግለዋል።
እድሜአቸው ለጡረታ ሲደርስም በ፳፻ ፲፩ ዓ.ም በጡረታ ተገልለው ለአገር ሰላምና አንድነት በጸሎት ፈጣሪአቸውን በመለመን ላይ እንዳሉ ዛሬ ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
ሥርዓተ ቀብራቸውም ነገ ታኅሣሥ ፲፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ከቀኑ ፰ሰዓት ከ፴ ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል ሲል የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል።
=====================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://buff.ly/3NFvWam
FaceBook:https://buff.ly/3UxZqJq
Telegram:https://buff.ly/3Tcx06A Website: https://buff.ly/3DETCqV
Twitter:https://buff.ly/3E6WI8x
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
ንሥር ብሮድካስትን በወዳጅነት ይከታተሉን።
