
በወቅታዊጉዳይላይከእናትፓርቲየተሰጠመግለጫ
በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር መብት እንጂ ሊሰጥም ሆነ ሊነፈግ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንንም የተቃወመም ሆነ የነቀፈ የለም፤ ይልቁንም የበለጠ እያደገና እየሰፋ እንዲሄድ መበረታታት ያለበት በጎ ጅምር ነው ብለን እናስባለን። ይኹን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማችን በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር በቋንቋ ከመማር ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የሌለ ሲሆን በይዘቱም በሀሳቡም ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ነው። አዲስ አበባ እራሷን በራሷ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብት በማያሻማ ኹኔታ የተሰጣትና የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ መዲና እና የኹሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ ናት።
ከተማችን ከእኛ አልፎ የአፍሪካ መዲናና የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ስትሆን ተጠሪነቷም ለፌዴራሉ መንግሥት እንጂ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ይመስል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሮሚያ ክልል መዝሙርን ካልዘመራችሁና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ካልሰቀላችሁ በሚል በከተማ አስተዳደሩና የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አማካኝነት የተፈጸመው ተግባር ሕጋዊ መሠረት የሌለው፣ በሕጸናት ተማሪዎች ላይ የአካል መጎዳትና የመንፈስ ስብራትን ያስከተለ፣ ብዙ ንብረት እንዲወድም ምክንያት የሆነ፣ በመምህራንና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች እና በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ሥጋትን የጣለ አኩይ ተግባር ነው።
ከተማ አስተዳደሩ በፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት ከማፈርና የከተማችንን ሕዝብ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮኻል እንዲሉ የቀድሞው ሥርዓት የሚነቀፍበትን ከተጠያቂነት የማምለጫ የጦስ ዶሮ ፍለጋ አካሄድ በመጠቀም የችግሩን ባለቤት “የሰላም ስምምነቱ ያልተዋጠላቸው አካላት፣ ምእራባዊያን፣ አንዳንድ ጽንፈኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውጪም ከውስጥም በመተባበር የፈጸሙት ነው” በሚል ሕዝብን ማወናበድ ትዝብት ውስጥ የሚያስገባ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝብን መናቅ ብሎም የሌሎች ጉዳይ አስፈጻሚ አደረጎ መቁጠር፣ ችግሩን መሸፋፈንም ሆነ የችግሩ ፈጣሪ ላልሆነ አካል መስጠት መፍትሔ ሊሆን አይችልም፤ ከተጠያቂነትም አያስመልጥም። ስለሆነም
፩. የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን እንደፖለቲካ መሣሪያ ከመጠቀም እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ ከሚያጋጭ ሕገ ወጥ ደርጊቱ እንዲቆጠብ፤ ሕዝብንም በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ እናሳስባለን።
፪. በርዕሰ መምህራን፣ መምህራንና ተማሪዎች ላይ እያደረሰ ያለው ማዋከብና ማሸማቀቅ እንዲቆም፣ የታሰሩ ተማሪዎች እና መምህራንም ያለልዩነት በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።
፫. ፓርቲያችን የአዲስ አበባ ሕዝብ ያሳየውን ትእግስት እያደነቀ የከተማችንን ሰላም ከመቼውም በላቀ ኹኔታ በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ::
እናት ፓርቲ
ታኅሣስ ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

