
አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን ሲፒጄ የኢትዮጵያ ፖሊስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የበይነ መረብ ጋዜጠኛ መስከረም አበራን እንዲለቅና በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳም እንዲያቆም ጠይቋል፡፡
ሲፒጄ ኢትዮ-ንቃት ሚዲያ የተባለ የዩቲዩብ ጣቢያ መስራችና አዘጋጅ የሆነችውን መስከረም አበራን፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት ታህሳስ 4/2015 በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏት መዘገቡ ይታወቃል።
መስከረም ከዚህ በፊትም በእስር ቤት ሳምንታትን እንዳሳለፈች ያስታወሰው ሲፒጄ ከሚዲያ ሥራዋ ጋር በተያያዘ በድጋሚ መታሰሯ እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ያለምንም ማዘግየት የክስ ሂደቱን በማቋረጥ ከእስር ሊፈቷት ይገባል ሲሆን፤ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሥራዋን ልትሰራ ይገባልም ብሏል፡፡
ሲፒጄ የመስከረምን ጉዳይ አስመልክቶ ለፍትህ ሚኒስቴር ኢ-ሜይል ብልክም መልስ አላገኘሁም ያለ ሲሆን፣ ለፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲም የኢ-ሚይል እና የጽሑፍ መልዕክት ቢልክም መልስ እንዳላገኘ አስታውቋል፡፡
መስከረም አበራ ታሕሳስ 6/2015 የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረበች ሲሆን፣ ፖሊስ “ሕገ-መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ በአዲስ አበባና በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን “ኢትዮ ንቃት” በተባለ የበይነ መረብ ሚዲያና የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መንገድ እንዲዘጋ በማድረግና የመከላከያ ሰራዊት እንዳይታዘዝ በመቀስቀስ ወንጀል ተጠርጥራለች” በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡
ክስ ለመመስረት በቂ የሰነድ ማስረጃ አለኝ ያለው ፖሊስ፤ የሰው ማስረጃ ለመሰብሰብ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ፍርድ ቤቱ 14 የምርመራ ቀናትን በመፍቀድ ለታሕሳስ 20/2015 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
መስከረም አበራ አሁን ስትታሰር ለኹለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግንቦት 2014 በመንግሥት የደኅንነት ሰዎች ከተያዘች በኋላ ለሳምንታት በእስር ላይ ቆይታ በ30 ሺሕ ብር ዋስትና መፈታቷ ይታወሳል፡፡
መስከረም አበራ ቀደም ሲል የምትታወቅበት ሙያዋ መምህርነት ሲሆን፤ ከዚህ ሙያዋ ጎን ለጎን በመገናኛ ብዙኃን በአካል በመቅረብና ጽሑፎች በማጋራት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትንታኔዎችን በማቅረብ የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት መቻሏ ይታወቃል፡፡
=====================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://buff.ly/3NFvWam
FaceBook:https://buff.ly/3UxZqJq
Telegram:https://buff.ly/3Tcx06A Website: https://buff.ly/3DETCqV
Twitter:https://buff.ly/3E6WI8x
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
ንሥር ብሮድካስትን በወዳጅነት ይከታተሉን።

