

መነሻቸውን ከሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ እና ኩታ ገጠም ከሆነው ከምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪረሙ ወረዳ ያደረጉ በርካታ የአማራ ተወላጆች የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ከከፈቱባቸው ጥቃት ለማምለጥ ወደ አማራ ክልል ሲሸሹ አባይ በርሃ ላይ ያደፈጡ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ከ17 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ከ17 በላይ የሚሆኑት ሰዎች የተገደሉት ታህሳስ 10/2015 ዓ.ም አመሻሹ ላይ ሲሆን ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ 12ቱ ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ ከአምስት በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ የአባይን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ሰጥመው መሞታቸውን ምንጮች ገልፀዋል።
በርሃው ውስጥ መሽገው የነበሩት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከከፈቱት ተኩስ ህይወታቸውን ለማትረፍ የአባይን ወንዝ በዋና ለመሻገር ሲሞክሩ ከሰጠሙት መካከል የአምስቱ ሰዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆን ተጨማሪ የሟቾችን አስከሬን ከወንዙ ለማውጣት አሁንም ፍለጋ ላይ መሆናቸውን የመረጃ ምንጮች ተናግረዋል።
የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች የአማራ ተወላጆችን ያነቃሉ ያደራጃሉ ብለው የጠረጠሯቸውን ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል ምክኒያት በሁለቱ የወለጋ ዞኖች ከከፈቱት ጥቃት እራሳቸውን ለመከላከል ወደ አማራ ክልል ሲሸሹ ከነበሩት የአማራ ተወላጆች መካከል አባይ በርሃ ላይ ደፍጠው የተቀመጡ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ከተገደሉት 12 ሰዎች እና ከዚህ ተኩስ ለማምለጥ የአባይን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ሰጥመው ከቀሩት ከአምስት በላይ ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ህፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ደብዛቸው መጥፋቱንም የአይን እማኞቹ አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን መካከል ከሚገኘው የአባይ በርሃ ሲደርሱ በታጣቂዎቹ ከተከፈተባቸው ድንገተኛ የተኩስ እሩምታ እንደ አጋጣሚ ተርፈው ወደ አማራ ክልል መግባት የቻሉ ውስን ሰዎችም የሚቀበላቸው፣ የሚያስጠልላቸው አጥተው ከባድ ችግር ላይ መውደቃቸውን ጠቁመዋል።
በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ፣ጃርዴጋ ጃርቴ፣ሆሮ ቡሉቅ በተባሉ ወረዳዎች እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪረሙ፣ጊዳ አያና፣ ሳሲጋ እና ሊሙ በተባሉ ወረዳዎች በተለይ ከህዳር 9/2015 ዓ/ም ጀምሮ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች የአማራ ተወላጆችን ያነቃሉ፣ያደራጃሉ ብለው የጠረጠሯቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል ሰበብ በከፈቱት ተኩስ 307 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን የዘገበው የአማራ ድምፅ ነው።
=====================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://bit.ly/3No0s7x
FaceBook:https://www.facebook.com/Nisirbroadcasting
Telegram:https://t.me/nisirbroadcasting Website: https://nisirbroadcasting.com
Twitter:https://twitter.com/NISIRInternati1
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
ንሥር ብሮድካስትን በወዳጅነት ይከታተሉን።