
በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከሰንደቅ አላማ ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ የታሰሩ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው የ700 ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈቱ የለሚ ኩራ አንደኛ ደረጃ ፍርድቤት ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም ንገር ግን ፖሊስ ከላይ ትዕዛዝ ካልመጣ አልፈታም ማለቱን የተማሪ ወላጆች ገልፀዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ በአዲስአበባ ትምህርት ቤቶች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ እድሜዋ ከ18 አመት በታች የሆነ አንድ ሴት ተማሪን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ተማሪዎች በከተማዋ የተለያዩ እስርቤቶች ታስረው እንደሚገኙ የተማሪ ወላጆችን መግለፃቸው ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በከተማዋ ትምህርት ቤቶች እንዲሰቀል መወሰኑን ከተቃወሙ ትምህርት ቤቶች መካከል በነፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የፍሬሕይወት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ይጠቀሳል።
በትምህርት ቤቱ ባለፈው ሳምንት በተነሳ ተቃውሞ አንዲት መምህርን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች ለእስር ተዳርገዋል።
የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በዕለቱ ከእስር ቢፈቱም፤ 10 የሚደርሱ ተማሪዎች ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
የተማሪ ወላጆች እንደገለፁት፡ ልጆቻችን እንዲፈቱ ፍርድቤቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ውሳኔ ቢሰጥም፤ ነገር ግን ፖሊስ ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ አልፈታም ማለቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በየካ አባዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ህዳር 30/2015 በተነሳ ተቃውሞ በርካታ ተማሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን በዕለቱ ከታሰሩ ተማሪዎች መካከል የኦሮሞ ብሔር የሆኑ ተማሪዎች ተመርጠው ተፈተዋል ሲሉ የተማሪ ወላጆች አረጋግጠዋል።
13 የሚደርሱ ቀሪዎቹ ተማሪዎች በለሚ ኩራ አንደኛ ደረጃ ፍርድቤት በትናንትናው ዕለት የቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድቤቱ እያንዳንዳቸው በ700 ብር ዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም ነገር ግን ፖሊስ ተማሪዎቹን ለመፍታት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ተብሏል።
ፖሊስ ይግባኝ መጠየቁን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያመራም፡ “ከላይ ይፈቱ የሚል ትዕዛዝ ስላልመጣልኝ ተማሪዎችን አልፈታም” ማለቱ ተሰምቷል።
ፖሊስ የፍርድ ቤትን ውሳኔ አለማክበሩን ተከትሎ በጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ወላጆች ተናግረዋል።
ወላጆቹ እንደገለፁት፡ ተማሪዎቹ የታሰሩት ለታዳጊዎች በሚሆን ስፍራ ሳይሆን አዋቂዎች በሚታሰሩበት ክፍል ውስጥ መሆኑ የሕግ አግባብን የተከተለ አይደለም ያሉ ሲሆን ከዚህ አልፎ የታሰሩበት ክፍል ንፅህናው እጅግ የወረደ በመሆኑ ለልጆቻችን ጤና አስጊ እና አሳሳቢ ነው ብለዋል ሲል የአማራ ድምፅ ዘግቧል።
=====================
ወቅታዊ ፤ ትኩስ እና የተሟላ መረጃዎችን ለማግኘት
Youtube:https: https://bit.ly/3No0s7x
FaceBook:https://www.facebook.com/Nisirbroadcasting
Telegram:https://t.me/nisirbroadcasting Website: https://nisirbroadcasting.com
Twitter:https://twitter.com/NISIRInternati1
Instagram:https://www.instagram.com/nisirbroadcasting
